አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የተገኘው ሰላም የአሸንዳ፣ የዓይኒዋሪና የማርያ በዓላትን ካለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ለማክበር ማስቻሉን የክልሉ ጊዜያዊ አሥተዳደር ርዕሰ መሥተዳድር ጌታቸው ረዳ ገለፁ።
በክልሉ ከነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲከበር የቆየው የአሸንዳ በዓል ዛሬ የጊዜያዊ አሥተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በመቐለ ከተማ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት አቶ ጌታቸው ባደረጉት ንግግር÷ በዓሉ በድምቀት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ የተገኘው ሰላምም የአሸንዳ፣ የዓይኒዋሪና የማርያ በዓላትን ካለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ለማክበር ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ባህሉን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍና እሴቱን ለሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች ያስተዋወቀበት በዓል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡