Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዐይኑ ብሌን ሊጠብቀው እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዐይኑ ብሌን ሊጠብቀው እንደሚገባ የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሃና አጥናፉ አስገነዘቡ፡፡

ከሰሞኑ ባጋጠመው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ የመንገደኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ በረራዎች እንዲሰረዙና እንዲራዘሙ መደረጉ ይታወሳል።

ኃላፊዋ በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ አየር መንገዱ ዓለም-አቀፍ ደረጃው የጠበቀ፣ ሥነ-ምግባር የተላበሰና ጥራት ያለው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ኩራት የሆነውን ተቋሙ መደበኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለደንበኞች ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው÷ በሚሰራቸው ሥራዎችም የበርካታ ስኬቶች ባለቤት የሆነ አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ከግምት በማስገባት ከሰሞኑ በነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ከትናንት በስቲያ ብቻ 42 ዓለም አቀፍ በረራዎች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፍ ባለመቻላቸው ለደንበኞችን ደኅንነት ሲባል አቅራቢያ ወዳሉ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲያርፉ መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡

የሀገር ውስጥ በረራዎችም በዚሁ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ መስተጓጎላቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ለአብነትም ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ በነበረው የሀገር ውስጥ የበረራ መርሐ-ግብር ወደ መቀሌ ተጉዘው የነበሩ ሁለት አውሮፕላኖች ማረፍ ሳይችሉ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ሦስተኛ በረራ ወደ መቀሌ ለማድረግ በዝግጅት ላይ የነበረው አውሮፕላን የአየር ሁኔታው ለደኅንነት አስጊ በመሆኑ አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ሳይነሳ በረራው እንዲሰረዝ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በጊዜው በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች ከበረራው መሰረዝ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ደኅንነት መመሪያን በሚጻረር መልኩ ያልተገባ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን አሰራሮችን በጥብቅ ዲሲፕሊን እንደሚተገብር ገልጸው÷ መሰል ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ሊታረሙ እንደሚገባና ማንኛውም መንገደኛ አሰራሮችን ሊያከብር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አየር መንገዱ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቱም ባሻገር በሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ በተለይም በዓላት ሲኖሩ የተጓዦችን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪና ግዙፍ አውሮፕላኖችን ጭምር በመመደብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሰሞኑን በትግራይ ክልል ለሚከበረው የአሸንዳ በዓል ወደ መቀሌ በቀን እስከ 11 በረራዎችን እየተደረገ መሆኑን በአብነት አንስተዋል።

አየር መንገዱ በሚሰራው ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገልግሎት ጥራትና የላቀ አፈጻጸም ተደጋጋሚ ሽልማቶች እያሸነፈ የሚገኝ ግዙፍ ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመሆኑም ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀሰውና ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት መሆን የቻለውን ይህን አየር መንገድ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዐይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ በደንበኞች የሚነሱትን ቅሬታዎችን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዴስክ በሁሉም ተርሚናሎች ውስጥ ማቋቋሙን ጠቁመው÷ ደንበኞች ቅሬታና ችግር ካጋጠማቸው በቅሬታ ማቅረቢያ ዴስኮቹ ማመልከት እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በቀጣይም አየር መንገዱ ለደንበኞች ደኅንነትና ምቾት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን በማንሳት÷ በተለይ የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳይ ላይ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግለሰቦች ደረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሥም የማጥፋት ዘመቻዎችን በማጋለጥ የሚዲያ አካላት ከአየር መንገዱ ጋር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.