ቻይና 3 ሺህ 200 ኪሎ ግራም የሚሸከም ሰው አልባ አውሮፕላን የበረራ ሙከራ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና 3 ነጥብ 2 ቶን (3 ሺህ 200 ኪሎ ግራም) ጭነት መሸከም የሚችል ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የተሳካ የበረራ ሙከራ በማድረግ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቧን አስታወቀች፡፡
“ኤስ ኤ 750 ዩ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰው አልባ አውሮፕላኑ÷ በሰሜን ምዕራብ ቻይና ሻንዢ ግዛት ሺአን ከተማ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ለ40 ደቂቃ የተሳካ የሙከራ በረራ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በዋናነት ለአካባቢያዊ የአየር ላይ ቁሳቁስ እና የተለያዩ ሸቀጦች አቅርቦት እንዲሁም የደን ቃጠሎ ሲከሰት ለእሳት አደጋ መከላከል አገልግሎት እንደሚውልም ነው የተገለጸው፡፡
በሁናን ሻንህ ሁዋዩ የሰው አልባ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ መመረቱን ያመላከተው የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ÷ 7 ነጥብ 5 ቶን ክብደት እንዳለው እና በ7 ሺህ 300 ሜትር ከፍታ ላይ መብረር ይችላል ብሏል፡፡
በአንድ ጊዜ የመብረር አቅሙ 2 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ሲሆን÷ በሠዓት 308 ኪሎ ሜትር እንደሚከንፍ ተገልጿል፡፡