አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ ህዝብ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ ህዝብ ነገ በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በነገው ዕለት የሚካሄደውን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በሚተከሉ ችግኞች እየጨመረ መጥቶ አስደናቂ እድገት እያሳየ ነውብለዋል።
በክልሉ በ2011 ዓ.ም በ2 ቢሊየን የተጀመረው የችግኝ ዝግጅት በ2016 ዓ.ም ከእጥፍ በላይ አድጎ ወደ 5 ነጥብ 472 ቢሊየን ደርሷል ነው ያሉት።
ዘንድሮን ጨምሮ ባለፉት 6 ዓመታት በአጠቃላይ 25 ነጥብ 202 ቢሊየን ችግኝ መዘጋጀቱን ገልጸው ፥ ግባችን እያደገ የመጣበት ሒደት የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል፣ ሥነ-ምህዳርን ወደ ቀደመ ይዞታው እንዲመለስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለንን ፅኑ ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።
የሚተከሉ ችግኞች ቁጥርም እየጨመረ መጥቶ የ2016 ዓ.ም እቅድ 23 ነጥብ 41 ቢሊየን መድረሱን ያነሱት አቶ ሽመልስ ፥ይህ እድገት የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ተፅእዕኖ እና ግንዛቤ በህዝብ ዘንድ እያደገ መምጣቱን አመላካች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በክልሉ ከመሬት ሽፋን አንፃር እስከ 2015 ዓ.ም 5 ነጥብ 33 ሚሊየን ሄክታር የደረሰ ሲሆን ፥ በዚህ ዓመት ከተያዘው 1ነጥብ 29 ሚሊየን ሄክታር ጋር አጠቃላይ የመሬት ሽፋን ወደ 6 ነጥብ 62 ሚሊየን ሄክታር እንደሚደርስ ተናግረዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞች የመጽደቅ ስኬት ከፍተኛ የነበረ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ያለፉት አምስት ዓመታት አማካይ የጽድቀት ምጣኔ 88 ነጥብ 5 በመቶ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡
ይህ ስኬት በአጠቃላይ የደን መልሶ ማልማት፣ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ለተገኘው ስኬት የህዝቡ ተሳትፎ ቁልፍ አስተዋፅዖ ማድረጉን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ በዚህ ዓመት 21 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በነገው ዕለት ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ- ግብርም የክልሉ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡