በጋምቤላ ክልል የዘላቂ መሬት አያያዝ ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም 2 የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ሃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን መቋቋም የሚቻለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሲገነባ ነው፡፡
መሬትን፣ ደንና የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ብሎም የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው÷በፕሮግራሙ የተሰሩ ሥራዎች ዘላቂ እንዲሆኑ ህብረተሰቡን ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ሲሸጋገር መልካም ውጤቶችን ማስቀጠልናቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡