በሶማሌ ክልል በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ ዝግጅት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀምበር ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልቃድር ረሺድ÷ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሀገር በቀልና ለቆላማ አየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ በ400 ቦታዎች 852 ሔክታር መሬት ላይ እንደሚከናወን መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከ145 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይም በድሬዳዋ አሥተዳደርም የሀገር አቀፉ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ዝግጅት መጠናቀቁን የአሥተዳደሩ የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ እና በከተማ አስተዳደሩ አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የቴክኒካል ቡድን ሰብሳቢ ኑረዲን አብደላ ተናግረዋል፡፡