የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚቢሽን በመጪው እሑድ ይመረቃል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የተገነባ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚቢሽን ማዕከል የፊታችን እሑድ የሚመረቅ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ ከነሐሴ 19 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ኤግዚቢሽኑ በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ የሚደረግ ሲሆን÷ በማስጀመሪያው ዕለት በግሉ ዘርፍና መንግስት ተሳትፎ የተገነባ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚቢሽን የሚመረቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ በተለያዩ የወጪ ንግድ ምርቶች ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ማሳየት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በንግድ ሳምንት ከወጭ ንግድ ማዕከሉ በይፋ መከፈት በተጨማሪ አቅራቢ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለሸማቾች ያቀርባሉ፤የፓናል ውይይቶች እንደሚደረጉ እና ለንግዱ ማህበረሰብ እውቅና የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ለመጪው በዓል 115 ሚሊየን ሊትር ዘይት በቀጣዮቹ ቀናት ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ኮሚቴ ተቋቁሞ በህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንስተው ÷እስካሁን ከ60 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።