አገልግሎቱ በጽሑፍ የሕግ ማስጠንቀቂያ በመስጠትና በፍ/ቤት ውሳኔ ከ351 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በጽሑፍ የሕግ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እና በፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ 351 ሚሊየን 385 ሺህ 63 ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ፡፡
ገቢው የተገኘው ውዝፍ ወርሐዊ የፍጆታ ክፍያ ካለባቸው ደንበኞች፣ በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ላይ ጉዳት ካደረሱ እንዲሁም ውል ነክ ከሆኑ እና ከሌሎች ክፍያዎች መሆኑን ተቋሙ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በተቋሙ ላይ 64 ሚሊየን 983 ሺህ 319 ብር ጉዳት ያደረሱ 314 የወንጀል ክሶች ተመሥርተው 71 ግለሰቦች በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ እያንዳንዳቸው ከ5 ወር ቀላል እሥራት እስከ 18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ በፍርድ ቤት ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል፡፡