ሳቢና ሾል በተባለው የደቡብ ቻይና ባህር አካባቢ በተከሰተው የመርከቦች ግጭት ሁለቱ ሀገራት እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
የቻይና የባህር ዳርቻ ጥበቃ ቃል አቀባይ ጌንግ ዩ÷ የፊሊፒንስ መርከብ ከህጋዊ ቀዘፋ ውጭ ሆነ ብሎ የቻይናን መርከብ ገጭቷል ብለዋል።
የፊሊፒንስ መርከቦች ከቻይና መንግስት ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ዥያንቢን ሪፍ በተባለው የደቡብ ቻይና ባህር አካባቢ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ገልጸው፤ የቻይና የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች በፊሊፒንስ መርከቦች ላይ ህጋዊ የቁጥጥር እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
የፊሊፒንስ ብሔራዊ የጠረፍ ግብረ ሃይል በበኩሉ÷ የፊሊፒንስ መርከቦች በደቡብ ቻይና ባህር በሚገኘው የሳቢና ሾል አቅራቢያ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የቻይና መርከቦች ጋር መጋጨታቸውን በመግለጽ ቻይናን ወንጅሏል።
በግጭቱ በሁለት የፈሊፒንስ መርከቦች ላይ ጉዳት ማጋጠሙን ገልጿል።
ቻይና ከፊሊፒንስ ፓላዋን ደሴት በስተምዕራብ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ሳቢና ሾል ደሴት የይገባኛል ጥያቄ ስታነሳ ቆይታለች፡፡
ፊሊፒንስ በበኩላ የሳቢና ሾል ደሴት የራሷ ይዞታ እንደሆነ እና በአካባቢው ቻይና ሰው ሰራሽ ደሴት ለመገንባት ፍላጎት አላት በማለት ስትገልፅ መቆየቷን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡