በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተከናወነው ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተከናወነው ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድር ትናንት ሌሊት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በውድድሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ፣ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትን አቶ ኢያሱ ወሰን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
በ75 ኪሎግራም መካከለኛ ሚዛን የሴቶች ውድድር ናይጄሪያዊቷ ፓትሬሽያ ማባታና ሞዛምቢካዊቷ ራዲ አደሲንዳ ግጥሚያ ናይጄሪያዊቷ ቡጢኛ በ6 ዙር በተደረገ ውድድር በድምር ውጤት አሸናፊ ሆናለች።
በወንዶች የ60 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ውድድር ኢትዮጵያዊው አቡበከር ሰፋን እና ጋናዊው ጆሴፍ ኮሜይ ባደረጉት ግጥሚያ ጆሴፍ ኮሜይ በ6 ዙር ድምር ውጤት አሸናፊ ሆኗል።
በሌላ ውድድር በ75 ኪሎግራም መካከለኛ ሚዛን ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ተመስገን ምትኩ ከሞሮኳዊው ያሲኔ ኢሎረዝ ጋር ተጋጥሞ በ6 ዙር ድምር ውጤት ተሸንፏል።
በወንዶች 48 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ሩሲያዊው ኢድመንድ ኩሁዶዮን ከሜክሲኮዊው ዳንኤል ቫላዴራዝ ጋር ውድድራቸውን ያደረጉ ሲሆን ሩሲያዊው ኢድመንድ ኩሁዶዮን በ8 ዙር ድምር ውጤት አሸንፏል።
በተመሳሳይ በወንዶች 48 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ውድድር ኡዝቤኪስታናዊው ኖዲርጆን ሚዝራክሜዶቭ ከካዛኪስታናዊው ቴምራትስ ዝሁስፖቭ ጋር ተገናኝቶ በ8 ዙር ድምር ውጤት መሸነፉን ኢዜአ ዘግቧል።
በወንዶች 51 ኪሎግራም ቀላል ሚዛን ውድድር ደግሞ ጋናዊው አሎቲ ቲዮፊለስ ከዛምቢያዊው ፓትሪክ ችንዬምባ ጋር ባደረጉት ውድድር ፓትሪክ ችንዬምባ በ4 ዙር ድምር ውጤት አሸንፏል።
በውድድሩ መዝጊያ ጨዋታ በወንዶች 80 ኪሎግራም ከባድ ሚዛን ታንዛኒያዊው ዩሱፍ ቻንጋላዌና የዲሞክራቲክ ኮንጎው ፒታ ካቤጂ ተገናኝተው ዩሱፍ ቻንጋላዊ በ8 ዙር ድምር ውጤት አሸንፏል።