Fana: At a Speed of Life!

በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በ620 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር 300 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ።

የትግበራ ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና የአሚአ ፓወር ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ ተፈራርመዋል።

በተመሳሳይ አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ የሚያመነጨውን ኃይል ለኢትዮጵያ ለመሸጥ የኩባንያው ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ(ኢ/ር) ተፈራርመዋል።

ተቀማጭነቱን በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ያደረገ በታዳሽ ኃይል ልማት፣ ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት በማመንጨት ለ25 ዓመታት ለኢትዮጵያ ለመሸጭ ነው ሥምምነቱን የፈጸመው።

አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫን ሙሉ በሙሉ በራሱ በመገንባት ያመነጨውን ኃይል ለኢትዮጵያ እንደሚሸጥ ነው በመድረኩ የተገለጸው።

ፕሮጀክቱ ከ4 ሚሊየን በላይ ቤተሰብ የኃይል ተጠቃሚ ከማድረጉም ባለፈ በዓመት ከ690 ሺህ ቶን በላይ የበካይ ጋዝ ልቀትን ይቀንሳል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ÷የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው ከአሚአ ፓወር ጋር የተደረገው ሥምምነት ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳያ ነው ብለዋል።

የአሚአ ፖወር ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ÷ የአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በአፍሪካ ቀንድ ግዙፉ መሆኑን ጠቅሰው ከኢትዮጵያ ጋር እንደዚህ አይነት ሥምምነት መፈራረማችን ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.