የመምህራንን ክብርና አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው -ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመምህራንን ክብርና አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ በሐሮማያ ዩኒቨርስቲ በክረምት መርሐ-ግብር የሚሰለጥኑ መምህራንን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ከሰልጣኞች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ መምህርነት የተከበረ እና የአንድ ሀገር የእድገት መሰረት በመሆኑ ይህን ታላቅ ሙያ ወደነበረበት ክብር ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም የመምህራንን አቅም መገንባት እና ኑሮውን ማሻሻል የግድ በመሆኑ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ከደመወዝ ጭማሪ ጀምሮ የመምህራን ባንክ እስከመክፈት የሚደርሱ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በመምህራኑ የሚከፈተው ባንክም ሙያውንና ኑሯቸውን ለመቀየር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡