ምክር ቤቱ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ 7 የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሰባት ዐበይት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጠ፡፡
በስብሰባው ላይ የምክር ቤቱን ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ-መሥተዳድሮች፣ የከተማ አሥተዳደር ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር፣ የክልልና የከተማ አሥተዳደር የአደጋ ስጋት ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።
ክልሎችና ከተማ አሥተዳደሮች በራስ አቅም ድጋፍን ለማሟላት እስከ አሁን የደረሱበትን ደረጃ እና ወቅታዊ ዘርፈ ብዙ አደጋዎች ክስተትና የሰብዓዊ ድጋፍ አፈፃፀም የተመለከተ ሪፖርት በስብሰባው ላይ ቀርቧል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሀገራዊ ደኅንነት እንዲሁም የክብር፣ የነፃነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ በመናበብ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በሪፖርቱ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ አቶ ተመስገን በአስቸኳይ ስብሰባው ላይ ቀጥለው የቀረቡትን ሰባት ዐበይት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ማስቀመጣቸውን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
1. ከተፈጥሮ አደጋ ውጭ ያሉ ተፈናቃይ ዜጎችን ወደ ነበሩበት በመመለስ፥ ለምርታማነት እና ማቋቋሚያ በሚሆን የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መስራት።
2. የተረጂዎችን እና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን የተጣራ መረጃ በመያዝ፥ የግል ማኅደራቸውን በጥንቃቄ በመለየት አደራጅቶ ማስቀመጥ።
3. ሀብትን በማሰባሰብ ረገድ ጥሩ አፈፃፀም ካሳዩ ክልሎች ተሞክሮ በመቅሰም ተቀራራቢ የሆነ አፈፃፀም ላይ ለመድረስ መስራት።
4. ቅፅበታዊ አደጋዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ቅንጅታዊ ንቃተ ህሊና ይዞ መዘጋጀት እና የመሬት አጠቃቀምን በህግ ማዕቀፍ ማስተሳሰር፥ እንዲሁም በዝናብ ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት።
5. በተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ የሆነ መፍትሔ በእቅድ ውስጥ በማካተት፥ የአደጋውን ቀጥተኛ ተጎጂዎች በማዕቀፍ ውስጥ ማካተት።
6. የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ እና እርስ በርስ የወንድማማችነት ባህልን ማጠናከር እንዲሁም ክልሎች የያዙትን የመተሳሰብ እሴት አስቀጥለው በመጓዝ አብሮነታቸውን ማጠናከር።
7. እቅዶችን በጊዜውና በወቅቱ በማጠናቀቅ የተጓተቱ እና የተንጠለጠሉ ስራዎችን መቅረፍ እንዲሁም በቀጣይ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በጠራ እቅድ ማከናወን።