ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ ሰላም ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላለች- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሶማሊያ ሕዝብ ሰላም ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስገነዘቡ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ሶማሊያ በአትሚስ ጥላ ስር ግዳጁን በስኬት ለተወጣው አንድ ሻለቃ ጦር በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ፈርፈር ወረዳ ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ውሳኔ በፊትና በኋላ ለበርካታ ዓመታት ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ በመላክ የሶማሊያን ሕዝብ የፀጥታ ችግር ተጋርታ ከአልሸባብ ጥቃት እንዲጠበቅ በማድረግ በገንዘብ የማይተመን ዋጋ መክፈሏን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ሻለቃው ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር መልካም ግንኙነት የፈጠረና የተመሰገነ መሆኑን አውስተው÷ አባላቱ በጀግንነት ለፈፀሙት ግዳጅ ማመስገናቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ሻለቃው ሲገለገልባቸው የነበሩ ትጥቆችንና ንብረቶችን ወደሀገር ቤት በማጓጓዝ ረገድም የምስራቅ ዕዝ አንድ ኮር አባላት በርካታ ተሽከርካሪዎችን በቅልፈት በማጀብ ከ368 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ተጉዘው በአጭር ጊዜ ላከናወኑት ተግባር አመስግነዋል፡፡