ዩክሬን ወደ ሩሲያ ድንበር ያደረገችው ግስጋሴ ዋሺንግተን ያልጠበቀችው እንደነበር ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ላይ ያደረሰችው ጥቃት በአካባቢው ያሳደረውን ተፅዕኖ እና የፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በአሜሪካ ያልተጠበቀ መሆኑ ተነገረ።
የዩክሬን የሩሲያን ድንበር አልፋ በብዙ ኪሎሜትሮች መዝለቋን ዋሽንግተን በግርምት እየተመለከተችው መሆኑ ተመላክቷል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ይህ ድንገተኛ ጥቃት ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴን እንዴት እንደተለወጠና ዩክሬን በአሜሪካ የቀረቡላትን የጦር መሣሪያዎች አጠቃቀም ላይ ዋሺንግተን የተጫወተችውን ሚና በተመለከተ እየገመገሙ ነው።
ድንገተኛ ወረራው ሩሲያንም ሆነ ምዕራባውያን መሪዎችን ያስደመመ ሲሆን÷ ዩክሬንን ለመጠበቅ ለተሰለፈው ምዕራባውያን ሰራሽ መከላከያም ከከፍተኛ ስኬቶቹ አንዱ እንደሆነለት ተገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደን የአሜሪካ እና ሞስኮን ፍጥጫ በማያባብስ መልኩ ዩክሬን ሩሲያን ከወረረቻቸው አካባቢዎች እንድታስወጣ አቅም ለመፍጠር በተደጋጋሚ ሞክረዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በተደጋጋሚ ግጭቱን በሩሲያ እና በምዕራባውያን መካከል የተፈጠረ ጦርነት አድርገው ለመግለጽ ይሞከሩ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደን በበኩላቸው ይህንን አመለካከት ለማጥፋት በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ግልጽ ገደብ ለማበጀት ጥረት ማድረጋቸው ተነግሯል።
ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ያደረሰችው ጥቃት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሩሲያ ላይ በውጭ ሀገር ወታደሮች የደረሰ ትልቁ ጥቃት በመሆኑ በነጩ ቤተመንግስት ጥያቄ ማጫሩን ቢቢሲ ዘግቧል።