በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፌዴራልና የክልል የህዝብ ተወካዮች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፌዴራል እና የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በጋራ የሚያከናውኑትን የህዝብ ውክልና ስራ በማስመልከት በወልቂጤ ከተማ እየተወያዩ ነው፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ በዚሁ ወቅት÷ የመንግስት ዋና የትኩረት አቅጣጫ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፤ ለተፈጻሚነቱ ሰፋፊ ህዝባዊ ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባላት በነበራቸው የህዝብ የውክልና ስራ 22 ሺህ 880 የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ በውይይቱ ለፌደራል እና ለክልል ተቋማት ጥያቄዎች መቅረብ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ የምክር ቤት አባላቱ በየደረጃው ላሉ አስፈጻሚ አካላት አቅርበው ግብረ መልስ እንደተሰጠባቸውም ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኮቹ በተገኘው አንጻራዊ ሰላም በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች የመንግስትን ስራዎች በተሳካ መንገድ መፈጸም እና ማስፈጸም አስችሏል ነው ያሉት።
ክልሉ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች መላውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉም አፈ ጉባኤዋ አስረድተዋል።
የፓርላማ እና የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በጋራ የሚያከናውኑት የህዝብ ውክልና ስራ ከነገ ከሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ዋና አፈ ጉባኤዋ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡