የህጻናትን መቀንጨር ማስቆም እንደሚገባ ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህጻናትን መቀንጨር በማስቆም የነገ የሀገርን እጣ ፈንታ ከወዲሁ ማስተካከል እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነትና የማስፋፊያ ምዕራፍ ስትራቴጂ ትግበራ፣ የስርዓተ ምግብና የአመጋገብ ስርዓት ፍኖተ-ካርታ እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ትግበራና የቀጣይ ዕቅዶችን የተመለከ ውይይት ”የዜጎች ጤና ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በድሬዳዋ እየተካሔደ ነው።
ውይይቱን የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፥ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑ ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ህጻናት በመቀንጨር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የሀገር ተስፋ ላይ ጥላ የሚያጠላውን የህጻናት መቀንጨርን መከላከል የትውልድና የሀገር ግንባታ በመሆኑ መንግስት በትኩረት እየሰራበት እንደሚገኝም ነው ያነሱት።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ዓላማዎችን ለመተግበር መንግስት ተገቢውን በጀት መድቦ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ለትግበራው የቀጣይ ስራዎች በፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የምግብና ስርዓተ-ምግብ ስትራቴጂን ከሌሎች ሀገር በቀል ንቅናቄዎች ጋር አስተሳስሮ መስራት እንደሚገባና እየናረ የመጣውን የጤና አገልግሎት ወጪን ለመከላከል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመራሩና ባለሙያው በትኩረት እንዲሰራም አሳስበዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፥ የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ለመተግበርም ሆነ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብርናው ከፍ ያለ ሚና ይጫወታል።
የግብርናውን ዘርፍ በፖሊሲ ደግፎ አሰራርን በማዘመን ምርትን በዓይነትና ጥራት አምርቶ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፥ ከ5 ዓመት በታች የሆኑና የቀነጨሩ 39 በመቶ፣ 11 በመቶ ደግሞ የቀጨጩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ እስካሁን የተሰራውን በጥሩ ተሞክሮ ይዞ በቀጣይ ሰፊ የጋራ ስራን እንደሚጠይቅ አንስተዋል።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ ከጀመረ ሥምንት ዓመታትን፤ የማስፋፋት መርሐ ግብሩ ደግሞ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል ነው የተባለው።
የሰቆጣ የቃል ኪዳን በ2007 ዓ.ም ወደ ትግበራ በመግባት እናቶች እና ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሚረዳ በዋናነትም ከ2 አመት በታች የሆኑ ሕጻናት መቀንጨርን በ2022 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ከሀገሪቱ ለማስወገድ ያለመ ስምምነት ነው።
በፍሬህይወት ሰፊው