Fana: At a Speed of Life!

የ15 ዓመቱ ትውልደ – ኢትዮጵያዊ የቆዳ ካንሰር ተመራማሪው ሔመን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቆዳ ካንሰር የሚፈውስ ሳሙና ለመፍጠር እየተመራመረ ያለው ታዳጊው ሔመን ወንድወሰን በቀለ የታይም መጽሔት የዓመቱ ምርጡ ታዳጊ አድርጎ በፊት ገጹ ይዞት ወጥቷል፡፡

ከኢትዮጵያውያን ወላጆች የተገኘ የ15 ዓመቱ ታዳጊ ሔመን÷ ከሀገሩ በአራት ዓመቱ ወደ አሜሪካ በመውጣት በሰባት ዓመት የለጋነት እድሜው ስለቆዳ ካንሰር አስከፊነትና መፍትሄውን ለዓለም ስለማበርከት ህልሙን ስንቅ አድርጎ ቆይቷል፡፡

ይህ ህልሙ እንዲሳካም በቤቱ ምርምር ለማድረግም የመረጣቸው ቀላል የቤት ውስጥ ሳሙናዎችን እና ኬሚካሎችን ሲሆን ፥ በራሱ ጥናት ሲያደርግ ለሦስት ዓመት መቆዬቱንም ነው ታይም መጽሔት ያስነበበው፡፡

ሆኖም ይህን ሲያደርግ ከቤተሰቦቹ ተደብቆ እንደነበርና በዚህም ሙከራው እሳት ሊነሳ እንደነበር ይናገራል፡፡

ከዚያ በኋላም ቤተሰቦቹ ለሳይንስ ያለውን ጥልቅ ፍላጎት በመገንዘብ ሊደግፉትና በርታ ሊሉት እንደቻሉም ነው የተገለጸው፡፡

ሔመን አሁን ላይ 15 ዓመቱ ሲሆን ፥ ዓለም ምርምሩንና የቆዳ ካንሰር ፈውስን ሊያመጣ ነው በሚል በጉጉት እየተጠበቀ ያለ ታዳጊ ተመራማሪ ሆኗል፡፡

በዚህም ባለፈው ጥቅምት ወር የ3 ኤም ኩባንያ እና የዲስከቨሪ ትምህርት በዉድሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሔመን ታዳጊ ተመራማሪ በሚል አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በሽልማቱም 25 ሺህ ዶላር ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን ፥ በዚሁ የተለያዩ የቆዳ ካንሰር ዓይነቶችን ለማከም ሳሙናን እንደመድሃኒት በመጠቀም ነው ተብሏል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ምርት ወደ ገበያ ከመምጣቱ በፊት ዓመታት ሊወስድ ይችላል ፤ ሆኖም ግን አሁን ላይ ታዳጊው ተመራማሪ ሕልሙን እውን ለማድረግ በባልቲሞር በሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የህዝብ ጤና ትምህርት ቤት በላብራቶሪ ውስጥ በመስራት እያሳለፈ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

አንድ ቀን የእኔ ሳሙና በሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብሎ ማሰብ በጣም የሚያስደንቅ ነው የሚለው ሔመን ፥ ይህን ጥናት የጀመርኩትም ለዚህ ነው ይላል፡፡

ታይም የ2024 የታይም ምርጡ ታዳጊ ሲል በፊት ገጹ ያወጣውም ለዚህ ከራስ-ወዳድነት ነጻ የሆነ ምኞት ነው ሲል በገጹ አስነብቧል፡፡

ሔመን በጠራራማ ጸሃይ ውስጥ የሚሰሩ የጉልበት ሰራተኞች ማየቱን ጠቅሶ ፤ ወላጆቹ በፀሃይ የፀሃይ መከላከያ ክሬም አለመቀባትና ተገቢ ልብስ መልበስ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የሚያስከትለውን አደጋ ሲገልጹለት እንደነበር ያስታውሳል፡፡

በዚህም ለፀሃይና የአልትራቫዮሌት ጨረር ለረጅም ሰዓት ተጋላጭ መሆን ለቆዳ ካንስር ተጋላጭ እንደሚያደርግ መረዳት መቻሉንም ነው የሚገልጸው፡፡

በዚያ በለጋ እድሜው ሰዎች በቀላሉ ማግኘትና ራሳቸውን ከቆዳ ካንስር እንዲፈወሱ የሚችሉበትን የሳሙና መድሃኒት ለማግኘት ለሰዎች እፎይታ ምክንያት ለመሆን ጉዞ የጀመረው፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሔመን ከሥነ-ሕይዎት ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ቪቶ ረቤካ ጋር በመሆን የሳሙና መድሃኒቱን በአይጦች ላይ ሙከራ እያደረገ መሆኑንም ነው ታይም በገጹ ያስነበበው፡፡

ሆኖም ምርምሩ የባለቤትነት ፍቃድን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን እስኪያካትት ድረስ ዓመታታን ሊወስድ የሚችል ቢሆንም ፥ አስር ዓመት እንኳ ቢፈጅ ታዳጊው ሔመን 25 ዓመቱ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ይህ ማለት ደግሞ የህክምና ተማሪዎች ትምህርት አጠናቅቀው የሚጨርሱበት ዕድሜያቸውም እንዳልሆነ ገልጿል ዘገባው፡፡

በዚህም እድሜውን በአግባቡ የተጠቀመበት ታዳጊ አስብሎታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.