በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በ6 ግለሰቦች ላይ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በ6 ግለሰቦች ላይ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቀደ።
ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የክስ መመስረቻ ጥያቄንና የተጠርጣሪ ጠበቆችን የመከራከሪያ ነጥብ ተመልክቷል።
ተጠርጣሪዎቹ 1ኛ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሀብታሙ አበበ አጊሾ ( ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚና ምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ታምራት ታገሰ ተኮራ (ዶ/ር)፣ 3ኛ ኮንትራክተር የሆነው ደሳለኝ አስረዳ፣ 4ኛ የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ሙላቱ ኤርትሮ ጡንዳዳ፣ 5ኛ የዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ዳይሬክተር ማርቆስ ዮሃንስ ረገዮ እና የቀድሞ የአዋሽ ባንክ ሆሳህና ቅርጫፍ ስራ አስኪያጅ የነበረው መለሰ ግርማ ኤርጋኖ ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ደቡብ ቅርጫፍ መርማሪ የምርመራ ስራውን አጠናቆ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።
ከዚህም በኋላ የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በመዝገቡ ላይ ተሰይሞ ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን መነሻ ጉዳይ በዝርዝር ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቦ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
በዚህም ተጠርጣሪዎቹ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ለንግስት ኢሌኒ መታሰቢያ ሆስፒታል የኦክስጂን ማምረቻ ለማስገንባት መቀመጫውና ዋና መስሪያ ቤቱን ካናዳ ቶሮንቶ ካደረገ ኤ.ኤ.ኤም. ኢዲ ቴክኖሎጂ ኢንካ ለተባለ ድርጅት የመንግስትን የግዢ መመሪያው ባልጠበቀ መንገድ በአምስት አመት አፈጻጸሙ እየታየ መከፈል የሚገባውን አሰራር በመተላለፍ በውል ላይ የተዘረዘሩ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ባልተሰሩበት ሁኔታ ለድርጅቱ የ57 ሚሊየን 383 ሺህ 956 ብር ከ72 ሳንቲም ለታለመለት አላማ ሳይውል በመክፈል ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ፤
በተለይም የውል ማስከበሪያ የውሉን ጠቅላል ዋጋ 10 ከመቶ ማለትም 117 ሚሊየን 10 ሺህ 859 ብር ከ60 ሳንቲም የውል ማስከበሪያ ሳይቀርብ እና ስራውም በውል ላይ በተገለጸው ጊዜ ሳይጠናቀቅ በመቅረቱ ይህ የውል ማስከበሪያ ዋስትና ቀርቦ ቢሆን ኖሮ ለመንግስት ገቢ መደረግ የነበረበትን ጥቅም አሳጥተዋል በሚል የተጠረጠሩበትን ወንጀል ዐቃቤ ሕግ በክስ መመስረቻው ላይ በዝርዝር አቅርቧል።
በተጨማሪም ደሳለኝ አስረደ የግንባታ ስራ ተቋራጭ ደግሞ የመምህራን መኖሪያ ቤት 2 ህንጻ ግንባታ ስራ ግንቦት 2013 ዓ.ም እና ጥር ወር 2016 ዓ.ም በተገባው ውል መሰረት ለዚሁ ህንፃ ተቋራጭ በተጋነነ ዋጋ በመስጠት 272 ሚሊየን 170 ሺህ 210 ብር ከ60 ሳንቲም ያለአግባብ ለተጨማሪ የግንባታ ወጪ መደረጉ፤ ክፍያ በመፈጸም በዚህ ልክ በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ እና ለውለታ 26 ሚሊዮን ብር ጥቅም ማስገኘትና ማግኘት የሚል የጥርጣሬ መነሻም በዐቃቤ ሕግ በኩል ቀርቧል።
እንዲሁም በዝምድና እና በትውውቅ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ባለቤት እህት እና ሌሎች ሁለት ሰራተኞች ባልሰሩት ስራ በአበል መልክ የዩኒቨርሲቲውን ገንዘብ ያለአግባብ በመመዝበር ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሷል።
ተጠርጣሪዎች ከሌሎች እጃቸው ለጊዜው ካልተያዙ ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር በመንግስት ላይ 487 ሚሊየን 333 ሺህ 912 ብር ከ78 ሳንቲም ጉዳት እንዲደርስና ለሌሎች ያልተገባ ጥቅም እንዲያገኙ የተደረገ መሆኑን ጠቅሶ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል የተጣራባቸውና የምርመራ መዝገቡን ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ከመርማሪ ፖሊስ እንደደረሰው ለችሎቱ አቅርቧል።
የምርመራ መዝገቡ ውስብስብ መሆኑን የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ መዝገቡን በጥልቀት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ሰፋ ያለ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ያሉ እና ጉዳያቸው በአንድ መዝገብ የተጣራ በመሆኑ በአንድ ላይ ክስ ለማዘጋጀት በወ/መ/ስ/ስ /109 /1 መሰረት የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ዝርዝር የጥርጣሬ መነሻ ተጠርጣሪዎቹ የተሳትፎ ደረጃ ያልቀረበበትና በጥቅል ወንጀል ተፈጽሟል ተብሎ በደፈናው ክስ መመስረቻ ጥያቄ ሊቀርብ አይገባም በማለት ተከራክረዋል።
በዋናነት ዐቃቤ ሕግ ምርመራውን ሲመራ ቆይቶ እንደ አዲስ “የምርመራ መዝገቡን ተመልክቼ ለመወሰን እንድችል” ክስ የመመስረቻ ጊዜ ይፈቀድልኝ ማለቱ አግባብ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።
በተመሳሳይ ከአበል የወንጀል ተግባር ጋር በተያያዘ ሌሎች በዋስ በተለቀቁበት ሁኔታ ላይ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር የማይገናኙ ደንበኞቻችን በእስር እንዲቆዩ ተደርጎ የክስ መመስረቻ መጠየቁ ተገቢነት የለውም በማለት የተከራከሩ ጠበቆችም ነበሩ።
በጥቅሉ ደንበኞቻቸው ቋሚ አድራሻ ያላቸውና በየትኛውም ጊዜ ቢጠሩ መቅረብ የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የመመርመር ስልጣን ያለው ፖሊስ መሆኑን በመጥቀስ፤ ምርመራ መምራት ማለት የህግ ድጋፍ መስጠት ማለት መሆኑን ገልጾ መልስ ሰጥቷል።
ዐቃቤ ሕግ ተፈጽሟል ባለው የወንጀል ተግባር ጥቅም የተገኘበትና በመንግስት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን በመግለጽ የተጠረጠሩበት ወንጀል የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሰረት በከባድ ማለትም ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ በሚችል ድንጋጌ ስር ሊያስከስስ እንደሚችል ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ተከራክሯል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዛሬ ረፋድ ላይ ለክስ መመስረቻ ጊዜ መፍቀድ ተገቢ መሆኑን ገልጾ የተጠርጣሪዎችን ዋስትና በማለፍ ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ