Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ 40 በመቶ የሚሆነው በታላቁ ህዳሴ ተፋሰስ አካባቢ የሚተከል ነው- ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 40 በመቶ የሚሆነውችግኝ በታላቁ ህዳሴ ተፋሰስ አካባቢ የሚተከል መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በድሬዳዋ አሊ ቢራ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አከናውነዋል፡፡

አቶ ተመስገን በዚሁ ወቅት ÷ ድሬዳዋ ሞቃታማ መሆኗን ጠቅሰው ሙቀቷ ምቹ፣ አየሯም ተስማሚና ለአካባቢው ምቹ ሆና እንድትቀጥል ችግኞችን አብዝተን መትከል ይገባል ብለዋል።

ትልቅ ቦታ የትልቅ ሰው ስም በሚነሳበት የአሊ ቢራ ፓርክ የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም÷የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለየት የሚያደርገው ከተያዘው የ7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ 40 በመቶ የሚሆነው በታላቁ ህዳሴ ተፋሰስ አካባቢ የሚተከል በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ይህም የአባይ ወንዝና የታላቁ ህዳሴ ግድብን ከፍ ባለ አቅም ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው÷የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥም ሆነ አካባቢው ደጋግሞ የሚያጠቃውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከልና የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በከተማ አስተዳደሩ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ መተከሉን አስታውሰው በቀጣይ ቀናት 1 ሚሊየን ችግኝ በአንድ ጀምበር ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን አመላክተዋል።

በድሬዳዋ ከተማ አሊ ቢራ ፓርክ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.