የፋና ላምሮት የምዕራፍ 17 ውድድር ቅዳሜ ፍፃሜውን ያደርጋል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ላለፉት 3 ወራት ከአስደናቂ ተወዳዳሪዎቹ ጋር አብሯችሁ የቆየው የፋና ላምሮት የምዕራፍ 17 የድምፃዊያን ውድድር በመጪው ቅዳሜ ፍፃሜውን ያደርጋል።
ለፍፃሜው የደረሱት አራቱ ተፎካካሪዎች (አብርሃም ማርልኝ፣ ሱራፌል ደረጀ፣ ናሆም ነጋሽ እና ጴጥሮስ ማስረሻ) ሲሆኑ በዕለቱ በ3 ዙር የመረጧቸውን ሙዚቃዎች ከኮከብ ባንድ ጋር ያቀርባሉ።
በደማቅ ስነ-ስርዓት በሚካሄደው በዚህ የፍፃሜ ውድድር ላይ አንድ አንጋፋ ድምፃዊም በእንግድነት ይገኛል።
ለዚህ ውድድር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን÷ ለ1ኛ ደረጃ 400 ሺህ ብር፣ ለ2ኛ ደረጃ 300 ሺህ ብር፣ ለ3ኛ ደረጃ 200 ሺህ ብር እንዲሁም 4ኛ ደረጃን ለሚያገኝ ተወዳዳሪ የ100 ሺህ ብር ሽልማት ይበረከታል።
እነዚህ የምዕራፍ 17 የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች በቀጣይ አመት ለሚደረገው ለ5ኛው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በቀጥታ ማለፋቸውን ከወዲሁ አረጋግጠዋል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም አድማጭ ተመልካቾቹን የቅዳሜውን የፍፃሜ ውድድር በፋና ቴሌቭዥን፣ በፋና ኤፍ ኤም 98.1 እና በክልል ኤፍኤሞች፣ በፋና የፌስቡክ እና የቴሌግራም ገጾችን ጨምሮ በwww.fanabc.com ከ5፡30 ጀምሮ በቀጥታ ሥርጭት በመከታተል በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት የተወዳዳሪዎችን ኮድ በመላክ እየተዝናኑ እንዲደግፉ ጋብዟል፡፡
ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ መድረክ ያጡ ድምፃውያንን መድረክ እንዲያገኙ ያስቻለው የፋና ላምሮት ውድድር ከሚያስገኘው የገንዘብ ሽልማት በላይ ለተወዳዳሪዎች ቀጣይ የሙዚቃ ጉዞ ወሳኝ መነሻ ነው።
እንዲሁም ተወዳዳሪዎች በአድማጭ ተመልካች ዘንድ እውቅና እንዲያገኙ ያግዛል፤ ብዙዎችንም ያነቃቃል።
በለምለም ዮሐንስ