የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣን በሽታ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑን አወጀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት እየተስፋፋ ያለውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ሲል አውጇል፡፡
ቫይረሱ በኮንጎ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እየተስፋፋና ህጻናትና ጎልማሶች በበሽታው እየተያዙ መሆኑም ተሰምቷል፡፡
በአህጉሪቱ ያለው የክትባት መጠን ጥቂት እንደሆነ የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው።
በዚህ ሣምንት የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከላት (ሲዲሲ አፍሪካ) የዝንጀሮ ፈንጣጣ የህዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋ መሆኑንና ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች ሲያዙ፤ 524 ሰዎች በዚሁ ምክንያት መሞታቸውን በመግለጽ ዓለም አቀፍ ድጋፍ መጠየቁ ይታወሳል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፥ በሽታው ሁሉንም ሊያሳስብ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከአፍሪካ አልፎም የበለጠ የመስፋፋት እድሉ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
ሲዲሲ አፍሪካ በፈረንጆቹ 2024 በ13 ሀገራት ውስጥ በሽታው መከሰቱን ገልጾ፥ ቀደም ካለው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በበሽታው የተያዙ ሰዎች 160 በመቶ መጨመሩን አስታውቋል።
በበሽታው ምክንያት የሚከሰተው ሞት ደግሞ በ19 በመቶ ከፍ ማለቱም ነው የተገለጸው።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ የአደጋ ጊዜ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲሚ ኦርጋና እንዳሉት፥ ቀደም ሲል በሽታው ባልነበረባቸው ሀገራት እንደ ዩጋንዳ፣ ርዋንዳ፣ ብሩንዲ እና ኬንያ ባሉ ሀገራት መከሰቱ ተገልጿል።
በፈረንጆቹ 2022 በሽታው ሲከሰት ከ70 በላይ ሀገራትን ሲያጠቃ ከ1 በመቶ ያነሱ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ዘገባው አስታውሷል።