Fana: At a Speed of Life!

ታሽገው የነበሩ 22 ሺህ 717 ድርጅቶች የውል ስምምነት ፈጽመው ወደ አገልግሎት ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታሽገው የነበሩ 22 ሺህ 717 ድርጅቶች የውል ስምምነት እየፈጸሙ ዳግም ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ 4 ሺህ 408 ተቋማት መታሸጋቸውን፤ የአንድ ተቋም የንግድ ፈቃድ መታገዱን እና የአንድ ድርጅት ፈቃድ መሠረዙን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ 31 ምርት የደበቁ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን፤ የሦስት ተቋማት ንግድ ፈቃድ መታገዱን እና ሥድስት ነጋዴዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡

እስከ ዛሬ ታስረው ከነበሩ 704 ነጋዴዎች መካከል 190ዎቹ በድርጊታቸው በመጸጸታቸውና በሕግ አግባብ ብቻ ለመሥራት በመስማማታቸው ተፈትተዋል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የግንባታ ዕቃዎች ላይ እየተደረገ ባለው ክትትልና ቁጥጥር ሕገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 21 የሲሚንቶ፣ ሰባት የብረት፣ 10 የቆርቆሮ፣ ሦስት የሚስማር እና ሁለት የሴራሚክ ንግድ ተቋማት ታሽገዋል ብለዋል፡፡

በየጊዜው በተደረጉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ዘይት፣ በዱቄት፣ ስኳር፣ ቲማቲም፣ ድንችና የመሳሰሉት ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም ዋጋ የማረጋጋት ሥራው እንደሚቀጥል አመላክተው÷ በጤፍ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ እና ጥራጥሬ ምርቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ይጠናከራል ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.