Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ትርክትን ለማስረጽ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና የጎላ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጽንፍና ጽንፍ ያሉ የፍፁማዊ አንድነት እና የፍፁማዊ ልዩነት ትርክቶች ዋጋ እያስከፈሉ በመሆኑ ብሔራዊ ገዥ ትርክትን ለማስረጽ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚና የጎላ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የፌደራል ተቋማት አደረጃጀት አስተባባሪና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ “የብሔራዊነት ትርክት ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ ለፌደራል ተቋማት የኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቅቋል፡፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በማጠቃለያ መድረኩ የሥራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት÷ ሁለንተናዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ ለተጀመረው የሀገር ግንባታ ሒደት ጠንካራ ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ብዝኃነትን ማስተናገድ የሚችል ጠንካራ ሀገረመንግስት ለመገንባት ሚዲያ ከፍተኛ ሚና ስላለው÷ አሰባሳቢ ትርክቶችን ዕለታዊ አጀንዳ በማድረግ የአስተሳሰብና ተሻጋሪ የትውልድ ቀረጻ ላይ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

በተቋም ደረጃም አሰባሳቢ ትርክትን በቃል ከማቀንቀን ባለፈ በዕለት ተዕለት ስራዎች በተግባር መግለጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ለዚህም የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሰፊ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን የፓርቲው መረጃ አመላክቷል፡፡

በሀገራችን ጽንፍና ጽንፍ ያሉ የፍፁማዊ አንድነት እና የፍፁማዊ ልዩነት ትርክቶች ዋጋ እያስከፈሉ በመሆናቸው÷ የብሔራዊነት ገዥ ትርክት በሕዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች አበርክቶ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.