ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማኑዋል እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ለድንገተኛ አደጋዎች የተቀናጀ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፥ ከዚህ ቀደም ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት ማን በምን መልኩ መረጃ መስጠት እንዳለበት የሚያመላክት ግልፅ አሰራር እንዳልነበረ አስታውሰዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ ይሄንን ታሳቢ ያደረገ የቀውስ ጊዜ የኮሙኒኬሽን ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑን ነው የገለጹት።
እንደ ሀገር አደጋ ሲያጋጥም ከችግሩ በፍጥነት ለመውጣት በቅድሚያ ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እየተዘጋጀ ያለው የቀውስ ጊዜ የኮሙኒኬሽን ማኑዋል አደጋዎች ሲከሰቱ ከመበየን ጀምሮ ከፌደራል ጀምሮ እስከታች ባሉት መዋቅሮች የሚኖረውን ኃላፊነት በግልጽ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲም እያዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፥ የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማንዋል አንዱ ዘርፍ መሆኑን መናገራቸው የዘገበው ኢዜአ ነው።
ማንዋሉ አደጋውን ለመቀልበስ ማን በምን ጉዳይ ላይ መረጃ መስጠት እንዳለበት ግልጽ ማብራሪያ የተቀመጠበት መሆኑንም አብራርተዋል።
የቀውስ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ማንዋሉ ወጥ በሆነ ሀገራዊ ይዘት እየተዘጋጀ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ክልሎችና ተቋማት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የራሳቸውን ሰነድ ያዘጋጃሉ ብለዋል፡፡