Fana: At a Speed of Life!

በመካከለኛና ምዕራብ አፍሪካ የጎርፍ አደጋ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎችን ለችግር ዳረገ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛና ምዕራብ አፍሪካ የተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎችን ለችግር ተጋላጭ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ሪፖርት አመለከተ።

ይህ አሳሳቢ ሁኔታ የዝናብ ወቅት በገባ ሁለት ወራት ብቻ በቀጣናው በጣለው ከባድ ዝናብ እና ከፍተኛ ጎርፍ ምክንያት የተከሰተ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ከ700 ሺህ በላይ ሰዎችን ለችግር አጋልጧል ሲሉ የተመድ ዋና ጸሃፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃክ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

በመካከለኛ የአፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ኮትዲቯር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ማሊ እና ቶጎ ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ያሉባቸው ሀገራት እንደሆኑም ነው ያስታወቁት።

አደጋውን የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት ተመድ ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር ለተጎጂ ሀገራት መንግስታት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉም ተነስቷል፡፡

የቀረበው ድጋፍም የምግብ፣ የመጠለያ እና የውሃ እንዲሁም የንፅህና አገልግሎትን ያጠቃልላል ነው የተባለው።

የተመድ የማዕከላዊ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ በዚህ ዓመት 10 ሚሊየን ዶላር ለኮንጎ፣ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ለኒጀር መንግስታት መድቧል ተብሏል።

ይህ ድጋፍም ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በሚሊየን የሚቆጠሩ የሰው ልጆችን ህይወትን እያሰጋ የሚገኘውን የጎርፍ አደጋን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖዎችን ለመቀነስ ያለመ መሆኑን የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.