ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት እንዳትሰነዝር ምዕራባውያን ያቀረቡትን ጥሪ ውድቅ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን በእስራኤል ላይ ምላሽ እሰጣለሁ በሚል ካቀደችው የበቀል ጥቃት እንድትቆጠብ የምዕራባውያን ሀገራት ያቀረቡትን ጥሪ ውድቅ ማድረጓ ተሰምቷል፡፡
በቅርቡ ቴህራን ውስጥ የሐማስ የፖለቲካ ኃላፊ ኢስማኢል ሃኒዬህ መገደላቸውን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል ርምጃ እንደምትወስድ መዛቷ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ኢራን ወደ ርምጃ እንዳትገባ ብሪታንያን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጥሪ ያቀረቡ ቢሆንም÷ ቴህራን ጥሪውን እንደማትቀበለው አስታውቃለች፡፡
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ከኢራን ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዝሽኪያን ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት፥ እየታየ ያለው የወታደራዊ ጥቃት ስጋት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው “አጸፋ መውሰድ ወንጀልን የማስቆሚያ መንገድና የኢራን ሕጋዊ መብት ነው” ማለታቸውን የኢራንን መገናኛ ብዙኃን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እንዲሁም እስራኤል ወታደራዊ ኃይሏን በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን ማዘዟን፤ አሜሪካም በዚህ ሣምንት በኢራን ወይም በአጋሮቿ ለሚሰነዘረው ጥቃት በተጠንቀቅ ላይ መሆኗን ዘገባው አመላክቷል፡፡