Fana: At a Speed of Life!

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 3 አዳዲስ የሕጻናት ክትባት መሰጠት እንደሚጀምር ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ በኢትዮጵያ የሕጻናት የጉበት በሽታ መከላከያ፣ የቢጫ ወባ እና የወባ ክትባት መስጠት እንደሚጀምር ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ክትባቱን ለማስጀመርና ሂደቱን ለማሳካት ግብዓት የማሟላትና ፋይናንስ የማመቻቸት ሥራ መሠራቱን በሚኒስቴሩ የእናቶች ሕጻናትና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት ተጠባባቂ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዓለማየሁ ሁንዱማ ገልጸዋል፡፡

ክትባቶቹ በዘመቻ እና በመደበኛ መልክ እንደሚሰጡ ጠቁመው÷ እንደ ሀገር የጉበት በሽታን ለመቀነስ እና አስቀድሞ ለመከላከል ሕጻናት እንደተወለዱ ክትባቱ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

የቢጫ ወባና የወባ ክትባት እንዲሁም የኩፍኝ ክትባት ከዘጠኝ ወር ሕጻን ጀምሮ እስከ 59 ዓመት ላሉ ሰዎች በዘመቻ ይሰጣል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የወባ ክትባት ዕድሜያቸው ከአምስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ለሆኑ ሕጻናት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን በመግለጽ÷ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ሕጻናትን በማስከተብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.