የህፃናት አስም በሽታ መንስዔና ምልክቶች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አስም የመተንፈሻ አካላችን ባዕድ በሆኑ የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ቀስቃሽ ኬሚካሎች ተጽእኖ ምክንያት ከሚገባው በላይ በድንገት ለተወሰነ ጊዜ የቧንቧዎች መጥበብ ነው።
አሁን የምንገኝበት ወቅት ክረምትና ቅዝቃዜ የሚበዛበት በመሆኑ ህፃናት በቅዝቃዜ ምክንያት የሚባባስ የአፍንጫ አለርጂ እና የሳምባ አለርጂ ወይም የአስም በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቁበት ወይም የሚያዙበት ጊዜ ነው፡፡
የአስም በሽታ መነሻ ምክንያቶች:-
የአስም በሽታ በተፈጥሯዊ፣ አካባቢያዊ እና ቀስቃሽ በሆኑ ምክንያቶች ይነሳል።
የሚፈጠረው መስተጋብር የአየር ቧንቧን ለዘላቂ ቁስለት ወይም ብግነት በማጋለጥ አለርጂ ቀስቃሽ በሽታዎች ሲኖሩ የአየር ቧንቧ ከልክ ያለፈ ተለዋጭ ጥበት እና የቆሸሸ አየር ከሳንባ በሚፈለገው ልክ አለመውጣት ደግሞ ሳል እና የመታፈን ምክንያትን ያመጣል።
በቅዝቃዜ ወቅት እና ማታ ላይ የሚባባስ ደረቅ ሳል፣ የደረት መጨነቅ ወይም የመታፈን ስሜት፣ የትንፋሽ መፍጠን፣ የድካም ስሜት፣ የሰውነት መዛል እና ላብ፣ ሲር ሲር የሚል የትንፋሽ ድምፅ፣ ራስ ምታት፣ የትኩረት መቀነስ እና አቅልን መሳት የህመሙ ምልክቶች ናቸው።
ቤትን ከአስም ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮች ነጻ በማድረግ አስም እንዳይነሳ መከላከል፣ በቅዝቃዜ እና ጉንፋን በሚበዛባቸው ወቅቶች ደግሞ ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ የ አ.ብ.ክ.መ ጤና ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይ የህጻናት የመተንፈሻ ቱቦ በተፈጥሮ ጠባብ በመሆኑ ምክንያት ከአስም ጋር የሚመሳሰሉ ብዙ ህመሞች ስላሉ ከላይ የተጠቀሱት የህመም ምልክቶች ሲያዩ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማድረግ ይመከራል፡፡