የኢራን ባለሀብቶች በተሽከርካሪ መገጣጠም ዘርፍ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እሠራለሁ- ኤምባሲው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢራን ባለሀብቶች በግብርና ማቀነባበር እና በተሽከርካሪ መገጣጠም ዘርፍ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንሠራለን ሲሉ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር አሊ አክባር ገለጹ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሐ ይታገሱ (ዶ/ር) ከአምባሳደሩ ጋር ሀገራቱ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በኢንቨስትመንት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ኮርፖሬሽኑ በሚያሥተዳድራቸው የኢንቨስትመንት ማዕከሎች ባለሀብቶች ብዝኀነት እንዲኖራቸው እያደረገ በሚገኘው እንቅስቃሴ ኢራን ተሳታፊ እንድትሆን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠይቀዋል፡፡
ለዚህም የኢትዮ-ኢራን ኢንቨስትመንት ፎረም ማዘጋጀትን ጨምሮ ሌሎች አጋዥ ሥራዎችን በጋራ ማከናወን እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
አምባሳደሩ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለይም በኃይል ዘርፍ የታየው ተስፋ ሰጪ ውጤት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው÷ የኢራን ባለሀብቶች በግርብርና ምርት ማቀነባበር እና በተሽከርካሪ ማምረትና መገጣጠም ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንሠራለን ብለዋል፡፡