በ2017 ዓ.ም የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ይከናወናሉ – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በያዝነው የበጀት ዓመት የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የልማት ሥራዎች በትኩረት ይከናወናሉ ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
በዚህም የቱሪዝም ልማትን ለማጠናከር፣ ገቢን አሟጥጦ ለመሰብሰብ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለጤና አገልግሎት እና ትምህርት ጥራት ትኩረት እንደሚሠጥ አብራርተዋል፡፡
ከሕገ-ወጥ መሬት ወረራና ግንባታ ጋር በተያያዘ ሕግ የማስከበር ሥራ፣ የኮሪደር ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዐቢይ ትኩረቶች ናቸው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ የሚስችሉ ተግባራትን ጨምሮ የክልሉን ሰላም የማጠናከር ተግባራት በ2017 የበጀት ዓመት በልዩ ትኩረት እንደሚከናወኑ አመላክተዋል፡፡