አትሌት ታምራት ቶላ በአትሌቲክስ ወርቅ የለመደን ህዝብ ያስደሰተ ውጤት ማምጣቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓሪስ እየተካሄደ ባለው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አትሌት ታምራት ቶላ በማራቶን ያስመዘገበው ድል በአትሌቲክስ ወርቅ የለመደን ህዝብ ያስደሰተ ውጤት ማምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ ”በአዲስ ክብረ ወሰን የታጀበ ድል፣ በጀግናው ልጃችን አትሌት ታምራት ቶላ፣ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡
በአትሌቲክስ ውድድር ወርቅ የለመደን ህዝብ ጥማት ያረካ፣ ለጉጉቱም ምላሽ የሆነ እንዲሁም ቁጣና ቁጭቱን ያበረደ በአዲስ ክብረ ወሰን የታጀበ ታላቅ ድል በማግኘታችን በድጋሚ እንኳን ደስ ያለን ብለዋል፡፡
አትሌት ታምራት ቶላ 2፡06.26 በሆነ ሰዓት በመግባት የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸንፎ ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣቱ ይታወቃል።