Fana: At a Speed of Life!

በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ምክንት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል  ነባራዊ ሁኔታ የለም-  የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ምክንት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል  ነባራዊ ሁኔታ የለም ሲል  የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት በበጋ ስንዴ ልማት 107 ሚሊየን ኩንታል መሰብሰቡንና  በሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ ዐሻራም አመርቂ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጣዊ እና ውጫዊ  ተግዳሮቶችን በመቋቋም  ቀጣይነት ያለው እድገት በማስመዝገብ  አይበገሬነቱን ማስመስከሩን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷን አንስተው ጠቀሜታውን አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ ማሻሻያው ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማበረታታት እንዲሁም የታለመውን ፋይናንሻል መረጋጋት ግልፅነትን ለማሳደግ፤ የልማት ፕሮጀክት ውጤታማነትን እንዲሁም የመንግስትን ገቢን ለማሻሻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዙሪያ ያሉ ቭዥታዎችን ለማጥራት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በተለያዩ  ምሑራን በተለያዩ አማራጮች ማብራሪያ መሰጠቱንም አንስተዋል፡፡

በዚህም ማሻሻያው በታቀደለትና በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት በውጤታማነት እየተተገበረ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ የማሻሻያውን አስፈላጊነት በመረዳት በሚያስመሰግን አኳኋን የንግድ እንቅስቃሴውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል  ግን ተገቢ ያልሆኑ አዝማሚያወዎች እየታዩ ነው ያሉት ለገሰ(ዶ/ር) ህገ ወጥነትንና የራስን ስግብግብ ፍላጎትን በሌላው ላይ በመጫን ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና ምርትን ለመደበቅ የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልፀዋል፡፡

ይህ ድርጊት ምክንያታዊ መሰረት የሌለውና ተቀባይነት የለውም  ድርጊትነው ፤በዚህም  መንግስት የጀመረውን የቁጥጥር ስራ በማጠናከር የህግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ምክንያት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል  ነባራዊ ሁኔታ እንደሌለም አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም መንግስት በዓመቱ ህግና ስርዓትን ለማረጋገጥና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሰፋፊ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።

 

ነፍጥ ያነገቡ ሃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ ሁሉንም የሰላም በሮች ክፍት አድርጎ ጥሪ ማድረጉንና ድርድሮችንም ማድረጉን ተናግረዋል።

 

በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፥ በዚህም ከምርት ተስተጓጉለው የነበሩ አካባቢዎች ወደመደበኛ ህይወት መመለሳቸውን ገልጸዋል።

 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከነሃሴ 29  እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016ዓ.ም የመጀመሪያውን አፍሪካ ከተሞች ፎረም  እንደምታስተናግድና  በርካታ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል፡፡

 

የመክፈቻ ዝግጅቱም በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚካሄድ  ነው የተናገሩት፡፡

 

ፎረሙ ስኬታማ እንዲሆን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.