ኢትዮ ቴሌኮም በ305 የገጠር ቀበሌዎች ተግባራዊ የሚደረግ “የሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽን” ስራ አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም 305 የገጠር ቀበሌዎችን ተደራሽ የሚያደርግ “የሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽን ” ገንብቶ ስራ አስጀመረ ፡፡
የሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽን ግንባታዉ የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬ ህይወት ታምሩ በወላይታ ዞን ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ሾላ ኮዶ ቀበሌ በመገኘት የአገልግሎቱን መጀመር በይፋ አብስረዋል ።
በአገልግሎቱ የኔትወርክ ሽፋን ባልነበራቸው ገጠራማ አካባቢዎችየሚኖሩ 903 ሺህ ነዋሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የኔትዎርክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉንም ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ይህ ተግባር ኩባንያው የትኛውንም የማህበረሰብ ክፍል ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት እንዳይገለል ለማድረግ ያስቀመጠውን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥ ነውም ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚዋ ።
የሞባይል ኔትዎርክ መፍትሄዎች በቀላሉ የኔትወርክ አቅምን በማሳደግ የ2ጂ፣ የ3ጂ ፣ እንዲሁም እንደአስፈላጊነቱ የ4ጂ አገልግሎትን መስጠት የሚያስችል በሶላር ኃይል የሚሰራ ዘመናዊ ገፅታ የተላበሰ ሶሉሽን መሆኑም ተገልጿል ።
በምንተስኖት ሙሉጌታ