Fana: At a Speed of Life!

ኢንስቲትዩቱ በቀሪው የክረምት ጊዜ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀሪዎቹ የክረምት ወራት በመጠን እና በስርጭት ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት አስታወቀ።

በኢንስቲትዩቱ የትንበያ እና ቅድመና ማስጠንቀቅ ም/ዋና ዳሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፤ ክረምቱ በኤልኒና ተፅዕኖ ውስጥ በመሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ ውጪ ከባድ ዝናብ እንዲስተዋል አድርጓል።

ኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታ ትንበያ ለግብርና፣ ለውሃ እና ለአካባቢ ጥበቃ በጎ ተፅዕኖ ቢኖረውም ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የጥንቃቄ መልዕክት ለማህበረሰቡ፣ ለሚዲያዎች እና ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁን አስታውሰዋል።

አሁንም በቀሪዎቹ ወራት በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች እና ተፋሰሶች በመጠንና በስርጭት ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የአየር ሁኔታ ትንበያው ማመላከቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በተከዜ፣ በአባይ ዙሪያ እና ጣና፣ በላይኛው አዋሽ፣ በተንዳሆና ቆቃ ተፋሰሶች ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ ስለሚኖር የውሃ መጠንን ከፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

በአካባቢዎቹ ከሰሞኑ እንደተስተዋለው በመሬት መንሸራተት እና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ዜጎች እንዳይጎዱ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበዋል።

በማርታ ጌታቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.