አቶ ጥላሁን ከበደ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ በክልሉ የኢንቨስትመንት አቅም ዙሪያ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት ጋር በአርባምንጭ ከተማ ተወያዩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የክልሉ መንግስት የክልሉን ዕድገት እና ልማት ለማፋጠን ልዩ ትኩረት ካደረገባቸው ዘርፎች አንዱ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም፥ ክልሉ በርካታ ፀጋዎችና እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ክልሉን ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹና ተስማሚ በማድረግ ባሉት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ በርካታ ስራዎችን መስራቱንም አብራርዋል፡፡
የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ኦንጋዬ ኦዳ (ዶ/ር)፥ ክልሉ በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ መመቻቸቱን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ አባላት፥ በቀጣይ የክልሉን ኢንቨስትመንት አቅም ምልከታ በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች የቻይና ኢንቨስተሮች በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማስቻል ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ የቻይና ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱም ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነትና ትብብር በተለይ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱም መገለጹን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ መንግስት ክልሉን ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹና ሳቢ በማድረግ ተጨማሪ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በተለይ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና ሌሎች ዘርፎች ለመሳብ የህግና የአሰራር ማሻሻያ ማዕቀፎችን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡