ሱፍሌ ማልት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንቱን እንዲያስፋፋ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል- ኮርፖሬሽኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሱፍሌ ማልት ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለውን ኢንቨስትመንት እንዲያስፋፋ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቶማስ ኔቪውጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኩባንያው ስላለበት ወቅታዊ የምርት ሒደት፣ተኪ ምርትን ስለማሳደግና ስለ ወጪ ንግድ እንዲሁም በቀጣይ ኢንቨስትመቱን ማስፋፋት በሚቻልብት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር )÷በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው ሱፍሌ የብቅል አምራች ኩባንያ ኢንቨስትመንቱን እንዲያስፋፋ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ኩባንያው ኢትዮጵያ የቢራ ገብስ ብቅልን በአጭር ጊዜ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ላደረገችው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡
ሱፍሌ ማልት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተጨማሪ 2 ሄክታር መሬት መውሰዱን ጠቅሰው÷የኢንቨስትመንት ማስፋፊያውን እንዲጀምር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግለት ማረጋገጣቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል ፡፡
ኩባንያው በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ከ5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ተኪ ምርት ማምረቱ ተጠቁሟል።