ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ከኖርዌይ ምክትል የፍትህ ሚኒስትር ክርስቶፈር ሲቨርሴንን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚህ ወቅት የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ማጠናከር በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ የአ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የ2019 የአለም የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን ለመቀበል ሰሞኑን ኖርዌይ በቆዩበት ወቅት ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ይህ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ለማጠናከር የራሱ በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ዶክተር ማርቆስ ገልጸዋል።
ክርስቶፈር ሴቬስቲያን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የ2019 የአለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በዚህ ወቅት በነበራቸው ውይይት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት በሁሉም ዘርፍ በማጠናከር ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ተቀራርበው ለመስራት ተስማምተዋል።