ጃክ ሞተርስ በቅርቡ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠም ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ (ጃክ ሞተርስ) በቅርቡ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የመገጣጠም ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከጃክ ሞተርስ እና ሃዩጃን ኢንዱስትሪ ፓርክ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ጃክ ሞተርስ ከሃዩጃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር በጥምረት ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረትና መገጣጠም ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምቹ የፖሊሲ እና ገበያ ሁኔታ መመቻቸቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ተቋማቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያን ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ማምረት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የጃክ ሞተርስ አመራሮች በበኩላቸው÷ ኩባንያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠም ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ መወሰኑን እና በቅርቡም የኤሌትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠም ሥራ እንደሚጀምር አረጋግጠዋል፡፡