Fana: At a Speed of Life!

አደንዛዥ ዕፅ በመዋጥ ደብቃ ወደ ደቡብ አፍሪካ ልትጓዝ ስትል የተያዘችው ተጠርጣሪ ተከሰሰች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 120 ፍሬ ጥቅል አደንዛዥ ዕፅ በመዋጥ በሆዷ ውስጥ ደብቃ ወደ ደቡብ አፍሪካ ልትሄድ ስትል በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለችው ተጠርጣሪ ላይ ክስ ተመሰረተ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ካክሊ ፊይዝ የተባለች የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ያላት ግለሰብ ላይ በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተውን ክስ ተመልክቷል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ግለሰቧ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 525 ንዑስ ቁጥር 1 ለ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፏን አንስቷል፡፡

በዚህም እንዳይመረትና እንዳይዘዋወር በኽግ ክልከላ የተጣለበትን አደንዛዥ ዕፅ ለማዘዋወር በማሰብ በሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2:30 ወደ ደቡብ አፍሪካ ልትጓዝ ስትል በፌዴራል ፖሊስ ኤርፖርት ምድብ በነበሩ አባላት በጥርጣሬ በቁጥጥር ስር ውላ በተደረገባት የኤክስሬይ ምርመራ 1 ሺህ 80 ግራም የሆነ 120 ፍሬ ኮኬን አደንዛዥ ዕፅ ውጣ በሆዷ ውስጥ በመገኘቷ በአደገኛ አደንዛዥ ዕፅ ማዘዋወር ወንጀል ተከሳለች።

ተከሳሿ ከጠበቃዋ ጋር በፍርድ ቤት ቀርባ አስተርጓሚ ተመድቦላት በተረኛ ችሎት የክሱ ዝርዝር እንዲደርሳት ተደርጓል።

የተከሳሽ ጠበቃ ዋስትና እንዲፈቀድላት መጠየቁን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሿ ቋሚ አድራሻ እንደሌላት ጠቀሶ ፤ በዋስ ብትወጣ የዋስትና ግዴታዋን አክብራ ልትቀርብ አትችልም በማለት ተከራክሯል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ተረኛ ችሎቱ ተከሳሿ ቋሚ አድራሻ የሌላት በመሆኗ እና ብትወጣ የዋስትና ግዴታዋን አክብራ አትቀርብም የሚለውን ግምት በመያዝ የዋስትና ጥያቄዋን ውድቅ አድርጓል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ የክስ መቃወሚያ ካላት ለመጠባበቅ ለጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.