ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የወባ መድኃኒት መውሰድ ለተለያየ ችግር ይዳርጋል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐኪም ያልታዘዘ የወባ መድኃኒትን መውሰድ የተለያዩ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የወባ በሽታ አምጪ ጥገኛ ተኅዋስ ዝርያ ልየታ ሳይደረግና የሕክምና መመሪያ በሌለበት የወባ መድኃኒት መጠቀም÷ ከመድኃኒት መጠን፣ የአወሳሰድ ጊዜና ዓይነት ጋር በተያያዘ ችግር ስሚያስከትል ከመድኃኒቱ የሚጠበቀውን ውጤት ማግኘት እንደማይቻል ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በአጠቃላይ የፀረ-ወባ መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መጠቀምም መድኃኒቱን የሚቋቋሙ የወባ ጥገኛ ዝርያዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ወደፊት የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም አስቸጋሪ ሁኔታ ያስከትላል ይላሉ፡፡
ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ የሚወሰዱ የወባ መድኃኒቶች ግለሰቡ ከሚወስዳቸው ሌሎች መድኃኒቶች ጋር አሉታዊ መሥተጋብር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መገለጹን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡
ይህም ጎጂ የጎንዮሽ ጉዳት እንዲከሰት ወይም የሕክምናው ውጤታማነት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ፤ የወባ በሽታ ያለበት ሰው መድኃኒት በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ ሕክምናውን መከታተል እንደሚገባው ይመክራሉ፡፡