መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ደብቀው በተገኙ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት እንዲፈጠር ምርት ደብቀው በተገኙ ህገወጦች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ምርቶችን በመደበቅ እና ሰው ሰራሽ የሸቀጥ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ በምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ስራ ለመስራት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እና ግብረ ኃይሉ በማክሮ የኢኮኖሚ መሻሻያ ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን ከመስራት ጎን ለጎን ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር ምርቶችን በሚደብቁ ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ባደረገው ክትትል በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 መጋዘን ሙሉ የምግብ ዘይት መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘይቱን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባው ድርጅት ምርቱን በወቅቱ ወደ ገበያ ማቅረብ እንዳለበት እና በጉዳዩ ዙሪያ አስፈላጊውን ማስረጃ እንዲሰጥ ተጠይቆ እንዳላቀረበና ዘይቱ ወደ ሌላ ስፍራ በማጓጓዝ ላይ እያለ ሦስት አይሱዙ በግብረ ኃይሉ አማካኝነት ተይዞ በተደረገ ብርበራ መጋዘን ሙሉ ዘይት እና ወደ ሌላ ስፍራ ሊጓጓዝ የነበረ 7 አይሱዙ የታሽገ ዘይት እንደተያዘና ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተደረገ ክትትል 8 ሺህ ባለ 3ሊትር እና 1ሺህ 924 ባለ አምስት እና 128 ባለ አንድ ሌትር ዘይት ተደብቆ መያዙ ተገልጿል፡፡
በክፍለ ከተማው ምርት የደበቁ ፣ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ያደረጉ 73 ንግድ ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡