አቶ ሽመልስ አብዲሳ የቦረና ከብት እንስሳት ዝርያ ማቆያ፣ ማዳቀያና ማደለቢያ ማዕከልን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የቦረና ከብት እንስሳት ዝርያ ማቆያ፣ ማዳቀያና ማደለቢያ ማዕከልን ጎበኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተጨማሪም በቦረና ዞን ኤልሮዬ ሳሪት አካባቢ በ63 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማን የእንስሳት መኖ አሰባሰብ ሂደት የተጎበኘ ሲሆን፤ በዞኑ በአጠቃላይ 650 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ እየለማ መሆኑ ተገልጿል።
እየለማ ያለው መኖ ምናልባት ድርቅ ቢያጋጥም ለሶስት ዓመታት ተቋቁሞ ማለፍን የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገር ይገባ የነበረን የመኖ ዘር በአካባቢው ማዘጋጀት መቻሉም ተነግሯል።
በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን ከማዕከሉ በተጨማሪ የያቤሎን አየር ማረፊያ የስራ ሂደትንም ተመልክቷል።
በመራኦል ከድር