ለ22 የከርስ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ውል ተፈጽሞ ወደ ሥራ መገባቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ለ22 የከርስ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶች የኮንትራት ውል ተወስዶ ወደ ሥራ መገባቱን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አፈጻጸምን ከክልል የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም ከፕሮጀክቱ ተወካዮች ጋር እየገመገመ ነው፡፡
የውሃ ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ ÷ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከሰው ሃይል ማሟላት ጋር በተያያዘ መጓተት ታይቶበት እንደነበር አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶችን ተግበራዊ ለማድረግ በተከናወነው የተቀናጀ ሥራ ባለፉት 6 ወራት የ22 ፕሮጀክቶች የኮንትራት ውል ተወስዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀዋል፡፡
አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ መግባታቸው የሚያበረታታ ነው ያሉት አማካሪው÷ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እና በጥራት ተገንበተው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አሳስበዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አማካሪና ምክትል አስተባባሪ ከበደ ገርባ (ዶ/ር) በበለኩላቸው ÷ በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት 110 የውሃ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም 1 ነጥብ 48 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡