ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 63 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው የ2 ሰዎች ህይወት አልፏል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 4 ሺህ 457 የላብራቶሪ ምርመራ 63 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፡፡
በዚህም በአጠቃላይ በሀገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 4 ሺህ 532 ደርሷል።
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 42 ወንዶችና 21 ሴቶች ሲሆኑ የእድሜ ክልላቸውም ከ14 እስከ 76 ዓመት ውስጥ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልፀዋል።
ከጠቅላላው የላብራቶሪ ምርምራ ውስጥ 18 ናሙናዎች በአስክሬን ላይ የተደረገ የላብራቶሪ ምርምራ ሲሆን ከአንድ የ75 ዓመት ወንድ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶበታል።
ከዚህ በተጨማሪ በለይቶ በህክምና ማዕክል ውስጥ ክትትል ላይ የነበረች የ34 ዓመት ሴት የአዲስ አበባ ነዋሪ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወቷ ያለፈ ሲሆን በጠቅላላ ሁለት ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ህይወታቸው አልፏል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 74 ደርሷል።
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት 91 ሰዎች 67 ከአዲስ አበባ፣ 16 ከሶማሌ ክልል፣ 4 ከአማራ ክልል፣ 2 ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እና 2 ከኦሮሚያ ክልል ያገገሙ ሲሆን በዚህም ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 213 መሆኑ ነው የተነገረው።