የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ለማስጀመር የቅድመ ምዝገባና ማረጋገጫ ሂደት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ለማስጀመር የቅድመ ምዝገባና ማረጋገጫ ሂደት መጀመሩን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደችውን የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማስቻል ያለመ ምክክር ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተካሂዷል።
በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተመራ ልዑክ በካናዳ ሞንትሪያል ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጁዋን ካርሎስ ሳላዛር ጋር በመገናኘት ምክክር ማድረጋቸውን አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ አመላክቷል።
በምክክሩም ዋና ዳይሬክተሯ ፥ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላትና ዓለምን በአገልግሎት እያስተሳሰረ ያለ ግዙፍ የአየርመንገድ ባለቤት መሆኗን አስታውሰዋል።
ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ድርጅት ከጉዞ ሰነድ የደህንነት ስራዎች ጋር በተያያዘ እያደረገ ላለው ድጋፍም አመስግነዋል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይም ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ስርዓት በምታደርገው የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠናን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፎች እንዲያደርግ ወ/ሮ ሰላማዊት ጠይቀዋል።
ጁዋን ካርሎስ በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ስርዓት ለመግባት ያሳለፈችውን ውሳኔ በማድነቅ በቀጣይ ተቋማቸው የማይቋረጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የኤሌክትሪክ ፓስፖርት ስርዓት እንድትገባ ለማድረግ የዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ልዑኩ በየብስ የድንበር ቁጥጥር ላይ ተግባራዊ የሚደረገው ቴክኖሎጂ ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ደረጃ ጋር የተጣጣመ መሆኑን የማረጋገጥ ምክክር ነው ከሚመለከታቸው የተቋሙ ኃላፊዎች ጋር ያካሄደው፡፡
በቀጣይ ቀናትም ተመሳሳይ ምክክሮች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል።