ያልተለመደው ክስተት የተፈጠረው በማዕከላዊ ፈረንሳይ ኦቤርቪለርስ ውስጥ ባለ አፓርታማ ነው፡፡
የአዕምሮ እድገት ውስንነት (ኦቲዝም) ተጠቂ የሆነው የ4 ዓመቱ ህፃን ኤንዞ ክፍሉ ውስጥ እያለ ያለቅሳል፡፡
ለቅሶውን የሰማው አባቱ እንደተለመደው ለማጣራት እና ልጁን ለማረጋጋት በፍጥነት ወደ ኤንዞ ክፍል ለመግባት ሲሞክር በሩ እንደተዘጋ ይረዳል፡፡
ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቀው ክስተት ግር የተሰኙት ወላጆቹ ልጁ በአጋጣሚ ራሱ ላይ ቆልፎ ይሆናል ሲሉ በፍርሃት ይዋጣሉ፡፡
ታዲያ ወላጅ አባቱ ጂ ልጁን ለማባበል በሩን ሰብሮ ሲገባም የኢንዞ ለቅሶ ቆሞ እና ክፍሉ ባዶ ሆኖ ይመለከታል።
የመስኮቱን ክፍት መሆን የተመለከተው አባት በከባድ ድንጋጤ ውስጥ ሆኖ ቁልቁል ወደመሬት ሲመለከት የህንፃው ምድር ቤት ባለ መድሃኒት ቤት ጣራ ላይ ልጁን አቧራ ለብሶ ተዘርሮ ይመለከታል።
ወዲያውም ጊዜ ሳያጠፋ ወደ ሥፍራው በፍጥነት ያቀናል፡፡
በኋላም 43 ሜትር ርቀት የወደቀው ህፃኑ ኤንዞ እግሩ ላይ ካጋጠመው ትንሽ ጭረት በስተቀር ምንም ሳይሆን ቆሞ በመራመዱ አባቱ በድንጋጤ እንደተመለከተው የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያመላክታል፡፡
ኤንዞ ራሱን ያውቅና ይራመድም ነበር ያለው አባትየው፤ በእግሩ ላይ ካለው ጭረት በስተቀር በውጫዊ አካሉ ላይ ምንም ጉዳት እንዳላየ በፈረንሳይ ለሚታተም አንድ ጋዜጣ ተናግሯል፡፡
በሁኔታው የተጨነቁት ወላጆቹ ድንገተኛ አገልግሎት ጠርተው ሆስፒታል ይወስዱታል፡፡
በሆስፒታልም ለሰባት ቀናት በተደረገለት ምርመራና ክትትል ወዲያው ከታከመው በኩላሊቶቹ እና ሳንባው ላይ ከተፈጠረ መጠነኛ መድማት ውጪ ኤንዞ ሙሉ ጤነኛ እንደሆነና እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ታይቶ እንደማይተወቅም ተገልፆላቸዋል፡፡
ለማመን በሚከብድ ሁኔታ አሁን ላይ ህፃኑ በሙሉ ጤንነት እንደሚገኝም ነው የተመላከተው።