ለ30 ዓመታት ያለእንቅልፍ …
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቬትናማዊቷ ሴት ለሦስት አስርት ዓመታት እንቅልፍ በዓይኔ ዞር አላለም ትላለች፡፡
ንጉየን ንጎክ ማይ ኪም ዕድሜዋ 49 ደርሷል። በትውልድ ሀገሯ ሎንግ አን ግዛት ውስጥ “የማታንቀላፋዋ ልብስ ሰፊ” በመባልም ትታወቃለች፤ ይህ ቅጽል ስምም ይስማማኛል ስትል በደስታ እንደምትቀበል ትናገራለች፡፡
እንቅልፍ አለመተኛቷ ጤናዋ ላይ ችግር እንዳላመጣባትም ትገልጻለች፡፡
ሆኖም ግን ቬትናማዊቷ ልብስ ሰፊ ያለ እንቅልፍ የመሥራት ችሎታዋ አብሮኝ አልተወለደም፤ ይልቁንስ ከልጅነቷ ጀምሮ ሌሊት ነቅታ ለመቆየት ጥረት ስታደርግ እንደኖረችም ነው የምትገልጸው፡፡
በመጀመሪያ ላይ በምሽት የማንበብ ፍላጎቷን ለማሳካት ነበር እንቅልፍ አጥታ የምታድረው፤ በኋላ የልብስ ስፌት ስራ ስትጀምር በደንበኞቿ የታዘዘችውን ልብሶች በወቅቱ ለማድረስ ነቅታ እንደምትቆይም ትገልጻለች፡፡
በዚህም እንቅልፍ በእኔ ህይወት ላይ ጠቀሜታ የለውም በማለት ከእንቅልፍ ከተለየች 30 ዓመታትን ማስቆጠሯን ነው የምትናገረው፡፡
ሆኖም ይህ ስኬት በቀላሉ አልመጣም ስትል በእንቅልፍ ማጣት ድብርት፣ ድካም እና ባስ ብሎም የትራፊክ አደጋ እንደደረሰባት ትገልጻለች፡፡
ሆኖም ለወራት ብሎም ለዓመታት ከእንቅልፍ ጋር ብርቱ ትግል በመግጠሟ ለ30 ዓመታት ለሸለብታ እንኳን አይኔን ጨፍኜ አላውቅም ስትልም ነው የምትናገረው፡፡
በአሁኑ ወቅት እንቅልፍ ልተኛ ብል እንኳን አልችልም ትላለች፡፡
የእንስቷ የእንቅልፍ ማጣት ችግር በህክምና ያልተረጋገጠ ቢሆንም፥ እሷ እንደምትለው ወሬውን ሰምተው ሌሊት ሊያዩዋት የሚመጡ ሰዎች እንዳሉና ይህም ዝነኛ አድርጓታል፡፡
ለዚህም ስትል ኪም የቤቷን በር ቀንና ሌሊት ክፍት ታደርጋለች፤ የእንቅልፍ ሰዓት የላትም፤ ምሽቶቿ በመብራቶች ደምቆ ለምትወደው የስፌት ስራዋ ብርሃንን እየለገሷት ይቆያሉ፤ የልብስ ስፌት መኪናዋ 24 ሰዓት ይሰራበታል፡፡ ጎብኚዎቿም ከሀገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች ወደ ቤቷ ይዘልቃሉ፡፡