Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ334 ሺህ ለሚበልጡ መዝገቦች ውሳኔ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ከ334 ሺህ ለሚበልጡ መዝገቦች እልባት መሰጠቱን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አብዬ ካሳሁን የ2016 በጀት ዓመት የ11 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ ጉባኤ ሲያቀርቡ እንደገለጹት፥ የዳኝነት አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም በየደረጃው ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች እንዲታዩ ከቀረቡ 387 ሺህ 143 መዝገቦች 86 ነጥብ 3 በመቶ ለሚሆኑት የፍትሃ-ብሔርና የወንጀል ጉዳዮች መዝገቦች እልባት መስጠቱን ገልጸው፤ አበረታች አፈጻጸም መኖሩን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ለሚያከናውኑት ስራ የምክር ቤት አባላት ድጋፍና ክትትላቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የክልሉ ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በችግር ውስጥ ሆኖ የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ የተሰራው ስራ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

የዳኞችን አቅም የማሳደግ ስራ መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፥ የዳኝነት ተደራሽነትን ለማስፋትና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የታየው ስራ መልካም መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፍርድ ቤቶች ጥራቱን የጠበቀ ውሳኔ እንዲሰጡ የምክር ቤት አባላት የሚያደርጉትን የድጋፍና ክትትል አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በፈፀሙት የዲሲፕሊን ጥሰት ከስራ እንዲሰናበቱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ያቀረባቸውን አራት የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች ምክር ቤቱ ተቀብሎ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.