Fana: At a Speed of Life!

2ኛው ዙር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ፓሪስ ገባ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያየ ርቀት ለወርቅ ሜዳሊያ የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ያካተተው ሁለተኛው ዙር የኦሊምፒክ ልዑክ ፈረንሳይ ፓሪስ ገባ፡፡

ትናንት ምሽት ከአዲስ አበባ የተነሳው ልዑኩ የአጭር፣ መካከለኛና ረዥም ርቀት ተወዳዳሪዎችን ያካተተ ነው፡፡

በልዑኩ ከተካተቱ አትሌቶች መካከልም÷ የ5 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ጉዳፍ ፀጋይን ጨምሮ ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ሐጎስ ገ/ሕይወት፣ ሰለሞን ባረጋ እና ፅጌ ዱጉማ ይገኙበታል፡፡

በዚህም በወንዶች 10 ሺህ ሜትር፣ 1 ሺህ 500 ሜትር እንዲሁም በሴት 800 ሜትር እና 5 ሺህ ሜትር የሚወዳደሩ አትሌቶች ፓሪስ መግባታቸውን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡

ልዑኩ ቻርልስ ደጎል አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና በፈረንሳይ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያን አቀባበል አድርገውለታል፡፡

በጉጉት የሚጠበቀውና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኙበት የ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድርም በአትሌት ምስጋና ዋቁማ ተሳታፊነት የፊታችን ሐሙስ ይካሄዳል፡፡

እንዲሁም ዓርብ የ800 ሴቶች፣ 5 ሺህ ሴቶች፣ 1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያዎች ሲካሄዱ÷ በዕለቱ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድር እንደሚካሄድ የወጣው መርሐ-ግብር አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.